
ወርቄ ሹምዬ
ዕድሜ (በቃለመጠይቅ ወቅት)፡- 45
ሆለታ ኢትዮጵያ
ረጋ ያለ ለዛ ያለው ባለ ዜማ ድምፅ ከስልኩ ውስጥ ይሰማል፡፡ ይህ ድምፅ በኢትዮጵያ ኦሮሚያ [1] ክልል የምትኖረው እናት፣ ሚስት እና አርሶአደር ወርቄ ድምፅ ነው፡፡ እናቷ ኦሮሞ ናቸው፣ አባቷ ደግሞ አማራ፤ እንደልማዱ ወርቄ አማራ ነች ብትባልም እሷ ግን አማራም ኦሮሞም እንደሆነች ታምናለች፡፡ ወርቄ ያላት የእርሻ መሬት ውስን ነው፤ ሆኖም በተለይ በጓሮዋ የተለያዩ ምርቶችን አሰባጥራ በተፈጥሮአዊ መንገድ በማምረት ያላትን መሬት በተቻላት መጠን ትጠቀምበታለች፡፡ ወርቄ በምታደርገው ያላሰለሰ ጥረት ራሷን ችላለች፤ የቤተሰቧንም የምግብ ዋስትና አረጋግጣለች፡፡ አራት ልጆቿን ከማሳደግ ጎን ለጎን ብዙውን ጊዜዋን ጓሮዋን በመንከባከብ ታሳልፋለች፤ ስታናግረን እንኳን በስራ እንደተጠመደች ነበር፡፡ ካደረግናቸው ተከታታይ ቃለመጠይቆች በአንዱ የእለት ስራዋን አቋርጬ ለጨዋታችን ረዘም ያለ ጊዜ ስለወሰድኩባት ይቅርታዋን ስጠይቅ “ምንም ችግር የለውም! ስናወራ ራሱ እኔ ስራዬን እየሰራው ነው፡፡ አረም እያረምኩ ስለሆነ አትጨነቂ፡፡ እኔኮ ስራ አልፈታም፡፡” ብላ ነግራኛለች፡፡
የተወለድኩት በ1964 ዓ.ም. በደቡብ-ምስራቅ ኢትዮጵያ ባሌ ክፍለ ሀገር ነው፡፡ አብዛኛው የልጅነት ጊዜዬ ያለፈው የደርግ መንግስት[2] መውደቅ ሲጀምር እና የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ሲገሰግስ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ በምኖርበት አካባቢ ሰላም መስፈን እንደጀመረ በደንብ አስታውሳለሁ፡፡
ከዚያ ቀደም የአካባቢያችን ወጣቶች ለውትድርና ይመለመላሉ ብለን በመስጋት እንኖር ነበር፤ የደርግ መንግስትንም በጣም እንጠላው ነበር፡፡ ደርግ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ግን ይህ ስጋታችን ተወገደ፡፡ በአንፃራነዊነት ሰላም ነገሠ፤ የወጣት ወንዶችም እጣ ፈንታ ተለወጠ፤ ትምህርት መማር የሚፈልጉም ትምህርታቸውን መማር ቻሉ፡፡
እኔን ያሳደጉኝ አያቶቼ ናቸው፡፡ አብልተው፣ አጠጥተው፣ አሳድገው ለቁም ነገር ያደረሱኝ እነሱ ናቸው፤ ስለዚህ እንደወላጆቼ የማያቸውም እነሱን ነው፡፡ እናቴ የወለደችን በልጅነቷ ነው፡፡ የእናቴ እድሜ በወቅቱ ስንት እንደነበር ባላውቅም በጣም ልጅ ከመሆኗ የተነሳ እኔን እንኳን የምታጠባው የጡት ወተት ማመንጨት እንዳልቻለች አያቶቼ ነግረውኛል፡፡ እናቴ በልጅነቷ ምክንያት እኔን ለማሳደግ ስላልቻለች የአባቴ እናትና አባት ወስደው በእርሻቸው ላይ አሳደጉኝ፡፡ አያቶቼ ገና ከተወለድኩበት ቀን ጀምሮ የላም ወተት እያጠጡ አሳድገውኛል፡፡
አባቴ እና እናቴ የተጋቡት ወላጆቻቸው ልጅህን ለልጄ ተባብለው ነበር፡፡ እኔ ከተወለድኩ ከጥቂት አመታት በኋላ ወላጆቼ ሌሎች ልጆችን ወልደዋል፤ አራት ወንድሞች እና አንድ እህት አለችኝ፡፡ የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ እኔ ነኝ፤ ከኔ ቀጥሎ አለማየሁ አለ፣ 44 አመቱ ነው፤ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ዘርአይ አለ 40 አመቱ ነው፤ የቤቱ አራተኛ ልጅ እና ብቸኛዋ እህታችን ሰብለ ነች፣ አምስተኛ ልጅ የሆነው ደረጄ ሲሆን እድሜው ደግሞ 34 አመት ነው፤ የሁላችንም ታናሽ ናትናኤል ይባላል የ25 አመት ወጣት ነው፡፡ ሰብለ፣ ደረጄ እና ናትናኤልን በልጅነታቸው እንከባከባቸው ነበር፡፡ ወንድሞቼ እና እህቴ ሁሉም በአባታችን በአቶ ተስፉ ስም ሲጠሩ እኔ ግን የምጠራው በአያቴ በአቶ ሹምዬ ስም ነው፡፡
ምንም እንኳን የአባቴ አባቱና እናቱ ቢያሳድጉኝም አባቴ ብዙም መጥቶ አይተይቀኝም ነበር፡፡ በወቅቱ በግብርና እና ገጠር ልማት ሚኒስቴር የግብርና ምርምር በሾፌርነት ይሰራ ስለነበር በአብዛኛው የሚኖረው ካምፕ ውስጥ ነበር፡፡ ወላጆቼ እና ወንድም እህቶቼ አዲስ አበባም ባሌም ቤት ስለነበራቸው አንዳንዴ አዲስ አበባ አንዳንዴ ባሌ ይኖሩ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወላጆቼን ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ የሄድኩት የ10 አመት ልጅ ልሆን ስል ነበር፡፡ ወላጆቼ ወደ ባሌ ሲመጡ እዛም እየሄድኩ እጠይቃቸው ነበር፡፡
ወንድሞቼ እና እህቴም ወደ ባሌ ሲመጡ አያቶቼ ቤት መጥተው ይጠይቁኛል፤ ሲመሽም ወደ ወላጆቻችን ቤት ይመለሳሉ፤ እኔ ግን ከአያቶቼ ጋር መሆን ስለሚሻለኝ እዛው እቀር ነበር፡፡ አንዳንዴ አዲስ አበባ እየሄድኩ ሌላ ጊዜ ደግሞ እነሱ ወደ ባሌ ሲመጡ ወላጆቼን ደጋግሜ የመጠየቅ እድል ነበረኝ፡፡
የተሻለ እርካታ የለም
ዘር እና ዘር ማንዘራችን በሙሉ አርሶ አደር እና አርብቶ አደሮች ነበሩ፤ ግብርና በደሜ ውስጥ አለ፡፡ አያቶቼ አጋርፋ[3] ላይ በትራክተር የሚታረስ ሰፊ መሬት አላቸው፤ በባሌ አካባቢ በተለምዶ የሚመረቱትን ስንዴ፣ ገብስ እና ማሽላ ያመርታሉ፡፡ ከዚህ መሬታቸው በሚያገኙት ገቢ ለራሳቸውም ሆነ ለኔ የተደላደለ ኑሮ መስርተዋል፡፡ አያቶቼ እድሜ ልካቸውን አርሰዋል፤ እኔ ግን ትልቅ ሰው እስክሆን ድረስ አንድም ቀን ዶማ እንኳን ነክቼ አላውቅም፡፡

በልጅነቴ ብዙውን ጊዜ የማሳልፈው ከወንድ አያቴ ጋር ነበር፡፡ አያቶቼ ቤት ያደኩ ብቸኛ የልጅ ልጅ እኔ ነኝ፡፡ አያቴ እራሱ እርሻ ባያርስም ስለእርሻ ብዙ ነገር ያውቃል፡፡ አስር ገበሬዎችን እና አራት የቤት ሰራተኞችን ቀጥሮ ያሰራ ነበር፡፡ ሰራተኞቹ ሲሰሩ አያቴ እየዞረ ይከታተላቸዋል፤ እንዴት እንደሚዘሩ እና እንደሚያጭዱ ያያል፤ እንዲሁም በአጠቃላይ ስራዎችን በአግባቡ እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡ ታዲያ እኔ በልጅነቴ አብሬው እየዞርኩ ሰራተኞቹ ሲሰሩ አይ ነበር፤ ከአያቴ ጋር የሚያደርጉትን የስራ ምክክር አዳምኝ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ሳላውቀው ስለግብርና ብዙ ነገር ተማርኩ፡፡ በልጅነቴ በእርሻ ውስጥ ከማደርገው አስደሳች ቆይታ እና ከማገኘው አዳዲስ ትምህርት ባለፈ የኔ ዋናው ስራዬ መብላት እና መጠጣት ነበር፤ እርጎ መጠጣት እና ማር መብላት በጣም ያስደስተኝ ነበር፡፡ በልጅነቴ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡
ምንም እንኳን አያቶቼ በምቾት አቀማጥለው ቢያሳድጉኝም ታታሪ ሰራተኛ እንድሆን ግን አድርገዋል፤ ጥሩ ምግብ እና የተመቸ ህይወት ከመስጠት ባለፈ ለስራ የተለየ አመለካከት እንዲኖረኝ እና በምችለው አቅም ሁሉ ስራ ሳልመርጥ እንድሰራ አድርገውኛል፡፡ ወንድ አያቴ አንድም ቀን ስራ እንድሰራ ጠይቆኝ ባያውቅም ስለ ስራ ስነ-ምግባር ግን አስተምሮኛል፡፡ አያቴ ታታሪ ሰራተኛ እንደሆነ አውቃለሁ:: የድካምን ፍሬ ከመብላት የበለጠ የተሻለ እርካታ የለም እያለም ሁል ጊዜ ይነግረኛል፡፡
የትዳር ህይወት … በጣም የተለየ እንደሚሆን
የ19 አመት ወጣት እያለሁ አባቴን ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ ሄድኩ፤ ያኔ ያየሁት የከተማ ሕይወት ስለሳበኝ እዛው ከአባቴ ጋር ለመኖር ወሰንኩ፡፡ በወቅቱ የባሌ ዘመዶች አባቴ የሚኖርበት አካባቢ ይኖሩ ነበር፡፡ አካባቢው ላይ ወጣ ገባ ስል ያዩኝ ስለነበር ለአባቴ እኔን እንዲድርላቸው ጥያቄ አቀረቡለት፡፡
በዚህም መሰረት በ20 ዓመቴ ተድሬ ከአባቴ ቤት ወጥቼ ከባለቤቴ ጋር መኖር ጀመርኩ፡፡ እንደተጋባን ከተማ አካባቢ ስለነበር ኑሮ የመሰረትነው ወዲያው የእርሻ ስራ መስራት አልጀመርኩም፡፡ አግብቼ መኖር የጀመርኩ ሰሞን ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ያለምንም ምክንያት ጭምር ቤቴን ጥዬ ወደቤተሰቦቼ ቤት በተደጋጋሚ እሄድ ነበር፤ በተለይ ባለቤቴ ትንሽ ካስቀየመኝማ በቃ ተነስቶ መብረር ነበር ስራዬ፤ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ልጅነት እና አለመብሰል እንደነበረብኝ ይሰማኛል፡፡
በኋላ አባቴ ጡረታ ሲወጣ ወላጆቼ ወንድሞቼና እህቴ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ በማሰብ በቋሚነት አዲስ አበባ መኖር ጀመሩ፡፡ በወቅቱ እኔ ከአዲስ አበባ 40 ኪ.ሜ. እርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ መኖር ጀምሬ ነበር፡፡
የትዳር ህይወት ስጀምር ትልቅ ለውጥ ያስተናገድኩበት እና አስቸጋሪ ነገር ያለፍኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ከባለቤቴ ጋር በደንብ ከመተዋወቅ ጀምሮ አዲስ የህይወት ዘይቤን እስከመልመድ ድረስ ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፌያለሁ፡፡ በልጅነቴ ወተት፣ ማር እና ቅቤ በተትረፈረፈበት ባሌ ላይ ባድግም ሆለታ ደግሞ ህይወት የተለየ ነበር፡፡
ሆለታ ወዳለው ቤታችን የገባን ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የጠጣሁት ቡና ትዝ ይለኛል፤ በጣም መራራ ነበር፡፡ እስከዛ ቀን ድረስ ቡና ካለ ወተት ባዶውን ጠጥቼ ስለማላውቅ በጣም መረረኝ፤ ጣዕሙ አሁንም አፌ ላይ አለ፡፡ ያቺ ቀን አዲስ የጀመርኩት የትዳር ህይወት ከአያቶቼ ጋር ከነበረኝ ኑሮ ጋር ሲነፃፀር በጣም የተለየ እንደሚሆን የተረዳሁበት ቀን ነበር፡፡
ከባለቤቴ ጋር የአማቾቼ መሬት ላይ መኖር ከጀመርን በኋላ ወንድ አያቴ በተደጋጋሚ እየመጣ ይጠይቀኝ እና አዲሱን ህይወት ያለማምደኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ልጄን ከወለድኩ በኋላ መረጋጋት እና ለትዳሬ መኖር ጀመርኩ፡፡ ከዛ በፊት ግን ለራሴ ምቾት እና ፍላጎት ብቻ እጨነቅ ነበር፡፡
አሁን ሁለት ሴት ልጆች እና ሁለት ወንድ ልጆች አሉኝ፤ የመጀመሪያው ልጄ 19 አመቱ ሲሆን የመጨረሻዋ ደግሞ ገና 3 አመቷ ነው፡፡ ሁለቱ ወንድ ልጆቼ እና አንዷ ሴት ልጄ ትምህርት ይማራሉ፡፡ የመጨረሻዋ ልጄ ገና ሶስት አመቷ ስለሆነ ትምህርት አልጀመረችም፡፡ ከወንድሞቼ እና ከእህቴ ጋር አሁንም አልፎ አልፎ እንጠያየቃለን፤ ልጆቼን እና እኔን ለመጠየቅ እናቴን ይዘዋት ሆለታ ድረስ ይመጣሉ፡፡
ከቁጣ ይልቅ ፍቅር
ባለቤቴ በጣም ይንከባከበኛል፤ ሳስቸግረው እንኳን ከቁጣ ይልቅ በፍቅር ይይዘኛል፡፡ በተለይ ገነ እንደተጋባን ሰሞን የነበረኝን ፀባይ ችሎ አብሮኝ ኖሯል፤ ባለቤቴ በጣም ይረዳኛል፡፡ በወጣትነቴ በተለይ ትግስት የለሽ መሆኔን የሚያውቁ እና ትዳር የጀመርኩ ሰሞን እንኳን በቤቴ ተረጋግቼ አንዳልተቀመጥኩ የሚረዱ ሰዎች ዛሬ ላይ በግብርና ስራ ተሳክቶልኝ ሲያዩ ይገርማቸዋል፤ ከፍተኛ ልፋት እና ያለመሰልቸት የሚጠይቅ የስራ መስክ ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየቴ ይደንቃቸዋል፡፡
ለቤተሰቤ ያለኝ ፍቅር ልብ እንድገዛ እንዳደረገኝ በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ የከፋኝ ቀን ባሌ “እስቲ ቁጭ በይ፤ አትጨነቂ፤ ቡና አፈላልሻለሁ፡፡” ይለኛል፡፡ ባሌ የሚያፈላልኝን ቡና እያዳንዷን ሲኒ አጣጥማታለው፤ በፍቅሩ ያረጋጋኛል፡፡
ትዝ ይለኛል 2003 ዓ.ም. ላይ ወንድ አያቴ ሊጠይቀን የመጣ ሰሞን ብዙ ድንች አምርተን ለሽያጭ አቅርበን ነበር፡፡ ታድያ አንድ ምሽት ቤተሰቡ እራት ለመብላት ሲሰበሰብ ድንቹን ቀቅዬ ለአያቴ አቀረብኩለት እሱም “የድካምን ፍሬ መብላት ምንኛ ደስ እንደሚል አየሽ?” አለኝ፡፡

አያቴ ለባለቤቴም እንደዚህ እራሴን ችዬ ማየት የሁልጊዜም ፍላጎቱ እንደነበረ ነገረው፡፡ በዚያች ቀን አያቴ ከላቤ ፍሬ ስለተመገበ በጣም ደስተኛ ነበር፤ በህይወቱም ሁሉ ለኔ ይመኘው የነበረውን ጥሩ ኑሮ በማግኘቴም ልቡ እንዳረፈ ነገረኝ፡፡
እኩል ነፃነት የላቸውም
ባለቤቴ ታጋሽ ሰው በመሆኑ እድለኛ ነኝ፡፡ ዛሬ ላይ ላለኝ የበሰለ ማንነት ምክንያቱ እሱ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜዬን ወይ ጓሮዬ ውስጥ ወይ ከልጆቼ ጋር ስለማሳልፍ ብዙ ጓደኞች የሉኝም፤ ማህበራዊ ኑሮ ላይ ግን በደንብ እሳተፋለሁ፤ አንዳንድ ጊዜም በመንደራችን ለሚገኙ ሴቶች የማማከር አገልግሎት እሰጣለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ ሴቶቹ ስለ ባሎቻቸው ያላቸውን አመለካከት አያለሁ፤ እንዴት አድርገው ባሎቻቸው እንደሚይዟቸውም እሰማለሁ፡፡ ብዙዎቹ ባሎቿቸውን ያማርራሉ፤ እኔ በቤቴ ከባሌ ጋር እንዳለኝ አይነት እኩል ነፃነት የላቸውም፡፡
በምሰራው ስራ፣ በማመርተው ምርት፣ ከምርቱም በማገኘው ገቢ እንዲሁም የገንዘቡ አጠቃቀም ላይ ባለቤቴ ጣልቃ አይገባም፤ ይህ መሆኑ ሰርቼ በማገኘው ገቢ የፈለኩትን ነገር የማድረግ ነፃነት እንዲኖረኝ አድርጓል፡፡
በሌላ መልኩ ሌሎች ባሎች ሚስቶቻቸው ላይ እንደሚያበዙት አይነት የስራ ጫና የለብኝም፡፡ በእኛ ቤተሰብ እንደሌላው ቤት ሁሉ ብዙ የሚሰራ የቤት ስራ አለ፤ እነዚህ ስራዎች ግን የኔ ብቻ ኃላፊነት አይደሉም፡፡ ባለቤቴ እና ልጆቼ በስራ ያግዙኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ኑሮ ለኔ ነፃነት ነው፤ በአካባቢዬ ያሉ ሌሎች ሴቶች እንደዚህ አይነት ነፃነት ስለሌላቸው አዝናለሁ፡፡
ማህበረሰቡም እንዲቀየር ምኞቴ ነው
እኔና ባለቤቴ ስንጋባ የንግድ ሥራ እንደምሰራ ተስማምተን ነበር፡፡ እሱም አልሳካ ሲል ትምህርቴን ቀጥዬ አንድ ቢሮ ውስጥ ተቀጥሬ እንድሰራ ባለቤቴ ይፈልግ ነበር፡፡ እኔ ግን እርሻ ላይ ነውና ያደግኩት የግብርና ስራ ለመስራት ወሰንኩ፡፡ ባለቤቴም ይህንን ሃሳቤን አልተቃወመኝም፡፡ ህይወቴን በሙሉ ብሰራው ብዬ የማስበው የግብርና ስራ መስራት በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
በአንድ ወቅት ባለቤቴ ቤት እንዳድስበት ብሎ 30000 ብር ሰጠኝ፤ እኔ ግን ለአትክልቶቼ ማጓጓዣ እንዲሆን ብዬ ጋሪ ገዛሁበት፣ ይህንን በማድረጌ ባለቤቴ አልተቃወመኝም፡፡ እርሻዬ እንዲያድግ እና እንዲስፋፋ እፈልጋለሁ፤ ከኔ ባለፈ ደግሞ በአካባቢዬ ያለው ማህበረሰቡም እንዲቀየር ምኞቴ ነው፡፡
ከልጅነቴ ጀምሬ ለራሴም ሆነ ለሌሎች የሚተርፍ ምርት የማመርትበትን ህይወት እፈልግ ነበር፡፡ እኔ እንደሌሎች ህፃናት የእናት ጡት አልጠባሁም፤ እኔ እየጠባሁ ያደግኩት የላም ወተት ነው፡፡ መሬት ለኔ እናቴ ናት፤ ከመሬት ጋር ያለኝ ግንኙነት ጥብቅ ነው፡፡

ሙሉ በሙሉ ወደመብኝ
ግብርና በ2000 ዓ.ም. ስጀምር እህል እና አትክልት አመርት ነበር፡፡ በወቅቱ የእህሉ ምርት አላዋጣኝም፤ እንደውም ብዙ አከሰረኝ፤ ያኔ ነበር ሙሉ በሙሉ አትክልት ወደማምረት የገባሁት፡፡
ከአምስት አመት በኋላ 2005 ዓ.ም. ላይ እርሻዬ በዋግ ተባይ ተመታ፡፡ እስከዛች ቀን ድረስ ድንች በስፋት አመርት ነበር፡፡ በወቅቱ ዋጉን የሚያጠፋ ፀረ-ተባይ እንዳለ አላውቅም ነበር፡፡ ስለ ፀረ-ተባዩ ከሰማሁ በኋላ ደግሞ ፈልጌ ለመግዛት ሶስት ቀን ወሰደበኝ፡፡ በዛ ላይ ፀረ-ተባዩን የሚረጭልኝ ሰው በማጣቴ በዋግ ምክንያት የድንች ምርቴ ሙሉ በሙሉ ወደመብኝ፡፡
ባለቤቴ ፀረ-አረም መርጨት ጎጂ እንደሆነ እና ካንሰር እንደሚያመጣ ስለሚያምን የሚረጭልኝ ሰው ሊያገኝልኝ ብዙ ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ እንደውም ባለቤቴ የኬሚካል ማዳበሪያ መጠቀም ያለውን ተጨማሪ ጉዳት ይነግረኝ እና ግብርናውን ሙሉ ለሙሉ እንድተወው ይገፋፋኝ ነበር፡፡ በወቅቱ በዋጉ ምክንያት በጠፋብኝ ምርት በጣም ተበሳጭቼ ነበር፤ በግብርናም ተስፋ እስከመቁረጥ ደርሼ ነበር፡፡
የማልጠቅምም መሰለኝ
የድንቼ ምርት ሲጠፋ ከዛ በፊት ለሶስት አመት ሰርቼ ባጠራቀምኩት ብር የገዛሁትን በሬ ለመሸጥ ወሰንኩ፡፡ ከበፊትም ጀምሮ ከአትክልት ምርት የማገኘውን ትርፍ መልሼ እርሻዬ ላይ ስለሆነ የማውለው በ2005 ዓ.ም. ድንቼ በዋግ ተመትቶ ሲጠፋ የነበረኝ ጥሪትም አብሮ ጠፋ፡፡ በዚህ ምክንያት በጣም ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡
በተጨማሪም በጣም ብዙ ላብ ያፈሰስኩበት ስራ ስለነበር ዙሪያው ጨልሞብኝ ነበር፡፡ ከዚያ ቀድሞ ከሁለት አመት በፊት አያቴ መጥቶ በስኬቴ እንደዛ እንዳልኮራብኝ በወቅቱ ሳይሳካልኝ በመቅረቴ በጣም አዘንኩ፤ የማልጠቅምም መሰለኝ፡፡
በወቅቱ መሬቴን ለእኩል አራሽ እስከ መስጠት እና ትርፉን መጋራት ድረስ አስቤ ነበር፡፡ አንድ አመት ሙሉ ምንም የእርሻ ስራ አልሰራሁም፡፡ በምትኩ ንቦች ስለነበሩኝ ማር ማምረት እና ዶሮዎች ማርባት ጀመርኩ፡፡ በዛው አመት መጨረሻ ነበር ስለ ዘላቂ ልማት መካነ ጥናት[4] ከሌሎች አርሶ አደሮች የሰማሁት፡፡ ድርጅቱ የተፈጥሮ ግብርናን እንደሚያስፋፋ እና አርሶ አደሩ በኬሚካል ማዳበሪያ እና ፀረ-ተባይ ፋንታ ኮምፖስትን እንዲጠቀም እንደሚያበረታታ ስሰማ አብሬያቸው ልሰራ ወሰንኩ፡፡
አዲስ የአመራረት ዘዴ
ከዘላቂ ልማት በማገኘው ስልጠና አካባቢን የማይጎዳ፣ ከኬሚካል ነፃ የሆነ የተባይ መቆጣጠሪያ እንዲሁም ተገቢ የመሬት አያያዝን የሚያበረታታ አዲስ የአመራረት ዘዴን ተማርኩ፡፡ የዘላቂ ልማትን የአመራረት ዘዴ ልቀበለው የቻልኩት ዘላቂ በመሆኑ እና ውድ የሆነ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ባለመጠቀሙ ነው፡፡ እነዚህን የአመራረት ዘዴዎች እንዴት በእርሻዬ ላይ እንደምተገብር ምክር እና የተግባር ስልጠና አግኝቻለሁ፡፡
ለረጅም አመት ባለማወቅ ለመሬቴ የሚገባውን እንክብካቤ አለማድረጌ ያሳዝነኛል፡፡ የኬሚካል ማዳበሪያ በመጠቀሜ መሬቴ በተፈጥሮ ያለውን ይዘት እንዲጠፋ አድርጌያለሁ፤ በተጨማሪም በወቅቱ መሬቴ እረፍት እንዲያደርግ እና እንዲያገግም አለማድረጌን ተረድቻለሁ፡፡
ከዘላቂ ልማት ጋር መስራት ከመጀመሬ በፊት ለበርካታ አመታት የኬሚካል ማዳበሪያ ለመጠቀም ብዙ ብር አወጣ ነበር፡፡ ማዳበሪያውን ለመግዛት ከማወጣው ወጪ በተጨማሪ ለሚረጭልኝ ሰው ክፍያ እከፍል ነበር፡፡ እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ የኬሚካል ማዳበሪያ እና ፀረ-ተባይ በከፍተኛ ደረጃ እጠቀም ነበር፡፡ በወቅቱ ስለተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም ስለማላውቅ ብዙ ገንዘብ ከስሬያለሁ፤ የእርሻዬ አፈር ለምነቱን አጥቷል፡፡
በዘላቂ ልማት እገዛ በዋጉ ከደረሰብኝ ጉዳት ማገገም ቻልኩ፡፡ ያን ሰሞን አንድ የድርጅቱ ሰራተኛ ጓሮዬን ልትጎበኝ በመጣች ጊዜ ከተከልኩት ጎመን በተጨማሪ በሶቢላ እንድተክል መከረችኝ፡፡ አዲስ ነገር ለመሞከር ዝግጁ ስለነበርኩ ምክሯን ተቀብዩ በሶቢላውን በ300 ካ.ሜ. መሬት ላይ ተከልኩት፡፡ በሚገርም ሁኔታ በሶቢላው ጥሩ ሆኖ አደገ፤ በወቅቱም 2000 ብር ሸጥኩት፤ ጎመኑን ደግሞ 3000 ብር መሸጥ ቻልኩ፡፡ ከሽያጩ ያገኘሁትን 5000 ብር ላም ገዛሁበት፡፡ ይህ ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘሁት ስኬት ነበር፡፡ አጋጣሚው ለእኔ የሚሆነኝን ትክክለኛውን የግብርና ዘዴ ያገኘሁበት እና ግብርና በደሜ ውስጥ እንዳለ ያመንኩበት ሁኔታ ነበር፡፡
እኔ መሬቴን ከተንከባከብኩት መሬቴ ደግሞ እኔን ይንከባከበኛል
አትክልት የማመርትበት መሬት ባለቤቴ ከቤተሰቦቹ የወረሰውመሬት ነው፡፡ የማመርታቸው ድንች፣ ካሮት እና ነጭ ሽንኩርትን የመሳሰሉ አትክልቶች ከማንኛውም አይነት ኬሚካል ነፃ ነው፡፡ መሬቱን ለማረስ ምንም አይነት ማረሻ አልጠቀምም፤ ሁሌም እራሴ በእጅ እቆፍራለሁ፡፡ ባለቤቴ የጤና ባለሙያ ስለሆነ እና ብዙ ጊዜ ስራ ስለሚውል በጓሮዬ ያለውን ሁሉንም ስራ የምሰራው እራሴ ነኝ፡፡
አትክልቶቼ ለኔ እንደ ልጆቼ ናቸው፡፡ ቀኑን በሙሉ ከነሱ ጋር እውላለሁ፤ ሲመሽም ሲነጋም ጓሮዬ እገኛለሁ፡፡ አንዳንዴ በበጋ ውሃ እጥረት ሲኖር ሌሊት እየተነሳሁ አትክልቶቼን ውሃ አጠጣለሁ፡፡ ባለቤቴ ከስራ ሲመለስ ውሃ በማጠጣት ያግዘኛል፡፡ ከቤቴ አይደለም ለቀናት ለሰዓታት እርቄ መሄድ አልወድም፡፡
ከአትክልቶቼ ጋር መሆን ያስደስተኛል፤ መሬቴ ለኔ ህይወቴ ነው፤ ለቤተሰቤ ደግሞ የኑሮአችን መሰረት ነው፡፡ እኔ መሬቴን ከተንከባከብኩት መሬቴ ደግሞ እኔን ይንከባከበኛል፡፡ መሬቴ ላይ የማመርተው ካሮት፣ ሴለሪ እና ቀይ ስርን የመሳሰሉ የተለያዩ የአትክልት አይነቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዳገኝ ይረዱኛል፡፡ በጓሮዬ ለምግብነት የሚሆኑ የተለያዩ አትክልቶችን ስለማመርት ከገበያ ብዙ ነገር አልገዛም፡፡
መኮትኮቻዬን ይቀሙኛል
ቀኔን በሙሉ ጓሮዬ ውስጥ አሳልፋለሁ፡፡ ጠዋት ልጆቼን አዘጋጅቼ ወደ ትምህርት ቤት እልካቸዋለሁ፤ ከዛ በኋላ ከብቶቹን ወደግጦሽ አሰማራለሁ፡፡
ከዛ በኋላ አትክልቶቼን መንከባከብ እጀምራለሁ፤ ልጆቼ ከሰአት በኋላ ከትምህርት ቤት እስኪመለሱ ድረስ አትክልቶቼን ውሃ አጠጣቸዋለሁ፤ እኮተኩታቸዋለሁ፡፡ ከትምህርት ቤት ከተመለሱ በኋላ ወንዱ ልጁ ምሳ ይሰራልኛል፤ ሴቷ ደግሞ ቡና ታፈላልኛለች፡፡ ያኔ ነው እኔም የጓሮ ስራዬን ተወት አድርጌ ወደቤት የምገባው፡፡
አንዳንዴ ያሰብኩትን ስራ ካላጠናከኩ ማረፍ ስለማልፈልግ ልጆቼ በግድ ጎትተው ወደቤት ያስገቡኛል፡፡ በጣም የባሰ እለት ልጆቼ መኮትኮቻዬን ይቀሙኛል፤ ወደቤትም እንድገባ እና ምሳዬን እንድበላ ያደርጉኛል፡፡ በበጋ ፀሃይ ከሆነ ከልጆቼ ጋር ምሳችንን እዛው ጓሮ ውስጥ እየሰራሁ እንበላለን፡፡
ምሳዬን ከልጆቼ ጋር ከበላን በኋላ ስራዬን እስኪመሽ ድረስ እቀጥላለሁ፡፡ አንዳንዴ ጓሮዬ ውስጥ በስራ ስጠመድ ለቅሶ መድረስ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን መሄድ እና ማህበራዊ ኖሩ ላይ መሳተፍ እረሳለሁ፡፡
ጓሮዬ ውስጥ የማሳልፈውን ጊዜ እንዳይሻማብኝ ማታ ማታ ወደ መኝታ ከመሄዴ በፊት ለልጆቼ ለሚቀጥለው ቀን ቁርስ የሚሆን ምግብ አበስላለሁ፡፡ አንዳንዴ እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ ምግብ ስሰራ አመሻለሁ፡፡ ምግብ ማብሰል ብዙ ሰዓት ቢፈጅም የተመጣጠነ ምግብ መመገብ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ለዛም ነው አትክልት የማመርተው፡፡
ልዩ ስሜት ይሰማኛል
ጓሮዬ ውስጥ ስሆን ልዩ ስሜት ይሰማኛል፡፡ ንቦቼ ያነጋግሩኛል፤ ምን አይነት አበባ እንደሚወዱ እና ጓሮዬ ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ይነግሩኛል፡፡ ዶሮዎቼ እና ከብቶቼም ያነጋግሩኛል፡፡ ሸረሪቶች የጎመን ተክሎቼ ላይ ሲሄዱ አያለሁ፡፡ ብቻ ሁሉም ነገር ይገርመኛል፤ ተፈጥሮ ያስደንቀኛል፡፡ ሁሉም ፍጥረታት በምክንያት አንደተፈጠሩ እንድረዳ ያደርገኛል፡፡ ወፎቹ ሲጠሙ ውሃ እሰጣቸዋለሁ፡፡ እኔ እንደምጠማው መጠማታቸው ይገርመኛል፡፡ ሁሉም ነገር ይደንቃል!
ጓሮዬ ውስጥ ስገባ ልገልፀው የማልችለው መአዛ ይሸተኛል፤ ሽቶ ሽቶ ይለኛል፡፡ ንቦቹ ተክሎች ላይ ሲያርፉ እና ወፎቹ መሬት ሲረግጡ ጓሮዬ በልዩ መዓዛ ይታወዳል፡፡ ለኔ ጓሮዬ ቢሮዬ አትክልቶቼ ደግሞ ደሞዜ ናቸው፡፡ ሽልማቴ እና የደስታዬ ምንጭ ናቸው፡፡ አሁን ያለሁበት ደረጃ ለኔ ገና መጀመሪያዬ ነው፤ እዚህ ላይ አላቆምም፤ ለብዙዎች ምሳሌ ለመሆን እፈልጋለሁ፡፡
የነበረኝን ጠንካራ አቋም

በአካባቢዬ የሚኖሩ ሰዎች አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን አብዛዎቹ መሬታቸውን አርሰው ከመኖር ይልቅ ሰፋፊ መሬት ላላቸው እና ማረስ ለማይፈልጉ ሰዎች ተቀጥረው የጉልበት ስራ ይሰራሉ፡፡ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶአደሮች በአቅራቢያችን ባለው የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ውስጥ የጉልበት ስራ በመስራት ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ፡፡ የምርምር ማዕከሉ እኔን ለመሰሉ አርሶአደሮች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከማዕከሉ ጋር ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በቅርበት እሰራለሁ፤ 2008 ዓ.ም ላይ በጓሮዬ የምሰራውን የእርሻ ስራ ለማበረታታት ግሪንሃውስ ሰርተውልኛል፡፡
የግብርና ምርምሩ ሰራተኞች ሁልጊዜ እየመጡ ይጎበኙኛል፡፡ በአንድ ወቅት ባለሙያዎቹ የኬሚካል ማዳበሪያ እንድጠቀም መከሩኝ፡፡ እኔ ግን በፍፁም ኬሚካል መጠቀም እንደማልፈልግ ነገርኳቸው፡፡ በተፈጥሯዊ መንገድ አትክልቶቼን ማምረት ካልቻልኩ የሰሩትን ግሪንሃውስ መውሰድ እንደሚችሉም ነገርኳቸው፡፡ የግብርና ምርምሩ ሰራተኞች በተፈጥሯዊ መንገድ ስለማምረት የነበረኝን ጠንካራ አቋም ስለተገንዘቡ ከዛ ወዲህ እንደፍላጎቴ እንድሰራ ትተውኛል፡፡
መሬት እስከሰጠችን ድረስ
ከመጨረሻው ህፃኑ ልጄ በስተቀር ሁሉም ልጆቼ ስለእርሻ ስራ ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ እኛ የምንኖረው መሬት እስከሰጠችን ድረስ ስለሆነ መሬትን በተቻለ መጠን መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ልጆቼ እንኳን ያውቃሉ፡፡
ልጆቼ ጥቅሙን ስላዩ እና ስላወቁ በተለይ የተፈጥሮ ግብርናን ይወዳሉ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሰው የኬሚካል ማዳበሪያ ሊሸጥልኝ ወደ ቤታችን ሲመጣ እኔ አፌን እንኳን ከመክፈቴ በፊት ልጆቼ ማዳበሪያውን እንደማንፈልግ ነገሩት፡፡ የሚያስከትለውን ጉዳት ጠንቅቀው ስለሚረዱ ልጆቼ የኬሚካል ማዳበሪያ እንደማያስፈልገን ያውቃሉ፡፡
በተለይ ትልቁ ልጄ አትክልት ማሳደግ ስለሚወድ በጓሮዬ ውስጥ ትንሽ መሬት ሰጥቼው የራሱን አትክልቶች ያመርታል፡፡ ሁለተኛዋ ልጄም ብትሆን የእርሻ ስራ ትወዳለች፤ በማንኛውም አጋጣሚ ለጉዳይ ከቤት እርቄ ስሄድ ልጆቼ እርሻውን በደንብ አድርገው መያዝ እንደሚችሉ አውቃለሁ፡፡
ድካም፣ ፅናት እና ትኩረት
በአካባቢዬ የሚኖሩ ሰዎች ጠንክረው ሰርተው ድህነትን እና ረሃብን እንዲያሸንፉ እፈልጋለሁ፤ አንዳንዶቹ የመሬት ችግር የለባቸውም፤ የራሳቸው መሬት ያላቸው እንኳን በራስ መሬትላይ ማረስ ድካም፣ ፅናት እና ትኩረት ስለሚፈልግ አርሰው መብላት አይፈልጉም፡፡ አብዛኛዎቹ የአካባቢዬ ነዋሪዎች መሬታቸውን ሸጠው ለሌሎች ሀብታም አርሶ አደሮች የጉልበት ስራ ይሰራሉ፡፡ እኔ ግን መሬታቸውን እንዳይሸጡ እመክራቸዋለሁ፡፡ ብዙዎቹ ተቀጥረው ሲሰሩ በወር በወር ገቢ ይገኛሉ፤ ይህ ደግሞ የራስን ሰብል ዘርቶ አመት ጠብቆ ከሚገኝ ገቢ ይሻላል ብለው ያምናሉ፡፡
እርግጥ ነው የምኖርበት ማህበረሰብ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የሚካድ አይደለም፤ ለምሳሌ በአካካቢያችን የውሃ እጥረት አለ፤ ነገር ግን አርሶአደሩ መሬት የማለማበት ውሃ በበቂ ሁኔታ የለም በማለት እርሻ ትቶ፣ መሬት ሽጦ ለሌሎች ሰዎች የጉልበት ስራ መስራት ተገባ አይደለም፡፡
ከድህነት ለመውጣት፣ እራሳችንን ለመመገብ እና ለሀገራችንም ለመብቃት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ሰዎች ሊጠይቁኝ ወደ ቤቴ ሲመጡ ሁሌም በጓሮዬ አትክልቶቼን ስንከባከብ ስለሚያገኙኝ ይገርማቸዋል፡፡ ሌት ከቀን ስለምሰራ ብረት ሴት ነሽ ይላሉ፡፡ የኔ ጥንካሬ የሚመነጨው ከቁርጠኝነቴ እና ከባለቤቴ እና ከልጆቼ ከማገኘው ድጋፍ ነው፡፡
ሰዎች እየተለወጡ
በአካባቢዬ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች እየተለወጡ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ሆኖም ከዚህ የበለጠ ማድረግ ይጠበቅብናል፤ የበለጠ መለወጥ፣ የበለጠ በርትቶ መስራት፣ እና የራሳችንን እርሻ ማረስ ይኖርብናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የተፈጥሮ ግብርናን በመጠቀም ማምረት ጀምረዋል፤ ለምክር እና ለአንዳንድ ድጋፍ ወደ እኔ ጋር ይመጣሉ፡፡
በቅርቡ የምናመርተው ሰብል በተደጋጋሚ በውርጭ እና በመጥፎ የአየር ሁኔታ ተመትቶብን ነበር፡፡ ውርጩ ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርስም በተፈጥሮ ግብርና የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ግን ጥፋቱን መቋቋም ችለዋል፡፡ ኬሚካል ማዳበሪያ ተጠቅመው እንደሚያመርቱ ሰዎች ሰብላቸው በብዛት አልወደመም፡፡
በተፈጥሮ ግብርና መርህ ማምረት የሚፈልጉ አርሶአደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም የኬሚካል ማዳበሪያ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ዛሬ ላይ ሰብላቸው ላይ የሚያጋጥማቸውን ተባይ ይዘው እየመጡ እንዴት ሊቆጣጠሯቸው እንደሚችሉ ከኔ ምክር መጠየቅ ጀምረዋል፡፡ በአካባቢዬ ያሉ ሀገር ሽማግሌዎችም በስርዬ ያደንቁኛል፤ ጥሬቴንም ያበረታታሉ፡፡ ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ ይጠቀምባቸው የነበሩ አሁን ግን ለአመታት የተዘነጉ ባህላዊ የተባይ መከላከያ ዘዴዎችን ፅፌ አስቀምጫቸዋለሁ፡፡
በአካባቢዬ የሚኖሩ ሰዎች በተለይ ሴቶቹ የቀን ሰራተኛ ሆነው ጉልበታቸውን ለሌሎች ከሚሸጡ አርሶአደሮች ቢሆኑ ምኞቴ ነው፤ ትልልቅ እርሻ ላላቸው ሰዎች ሰርተው የራሳቸው ባልሆነ ነገር ጥቂት ገንዘብን ከማግኘት ይልቅ ለቀን ስራ የሚያውሉትን ጉልበት የራሳቸው እርሻ ላይ አውለው ምርት ማምረት እና የራሳቸው የሆነ ነገር ቢኖራቸው እንደሚሻል ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ልክ እንደኔ የራሳቸውን መሬት አርሰው እና አለስልሰው ገቢ ማግኘት እና ጥሩ ህይወት መኖር ይችላሉ፡፡
ለውጥ ማምጣት እና መሬት ያጣችውን ልምላሜ መመለስ ይቻላል፤ ይሄ ደግሞ ጠንክሮ መስራትን ይፈልጋል፡፡ እኔ ከመሬት ጋር የነበረኝ ቆይታ፣ ከኬሚካል ማዳበሪያ ለመላቀቅ ያደረግኩት ትግል፣ በኋላም በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት አማካይነት የጀመርኩት የተፈጥሮ ግብርና ስራ መጪውን ግዜ መቀይር እንደምችል ተስፋ የሰጠኝ ሁኔታ ነው፡፡
- የኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዘጠኝ ክልላዊ መንግስቶች በስፋት ትልቁ ሲሆን በሀገሪቱ ቁጥሩ ከ30 ሚሊዮን የሚበልጥ የኦሮሞ ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል፡፡
- ደርግ ኢትዮጵያን ከ1966 እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ያስተዳደረው ወታደራዊ መንግስት አስተባባሪ ኮሚቴ መጠሪያ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሲሆን ግንባሩ በውስጡ አራት ፓርቲዎችን ይዟል፡፡
- አጋርፋ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የምትገኝ ወረዳ ስትሆን ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በ418 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
- ዘላቂ ልማት መካነ ጥናት የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን በ1988 ዓ.ም ትኩረቱን የገጠር አርሶአደር ማህበረሰብ ላይ አድርጎ ስራውን ጀመረ፡፡ ድርጅቱ የማህበረሰቡን የኑሮ ዘይቤ ለመደገፍ እና ለማሻሻል ዘላቂ እውቀት፣ ልማዶች እና ግኝቶችን የማስፋፋት እና የማበረታታት ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ እውነተኛ ተሳትፎ ላይ የተመሰረቱ የልምድ ልውውጦችን፣ ግልፅ ውይይትን፣ ምርምርን እና ስልጠናን መሰረት በማድረግ ምርጥ የሚባሉ የባህላዊ እና ዘመናዊ እውቀቶችን ያቀናጃል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ፡- http://www.isd-bio.org